14 የንጉሥ ቊጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤ጠቢብ ሰው ግን ቊጣውን ያበርዳል።
15 የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።
16 ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!
17 የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል።
18 ትዕቢት ጥፋትን፣የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።
19 በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣ከትዕቢተኞች ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል።
20 ምክርን የሚሰማ ይለመልማል፤ በእግዚአብሔርም የሚታመን ቡሩክ ነው።