7 ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ከሆዳሞች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን አባቱን ያዋርዳል።
8 በከፍተኛ ወለድ ሀብቱን የሚያካብት፣ለድኻ ለሚራራ፣ ለሌላው ሰው ያከማችለታል።
9 ሕግን ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው።
10 ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚመራ፣በቈፈረው ጒድጓድ ይገባል፤ንጹሓን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።
11 ባለጠጋ ራሱን ጠቢብ አድርጎ ይቈጥር ይሆናል፤አስተዋይ የሆነ ድኻ ግን መርምሮ ያውቀዋል።
12 ጻድቃን ድል ሲነሡ ታላቅ ደስታ ይሆናል፤ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ግን ሕዝብ ይሸሸጋል።
13 ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።