11 ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ።
12 እነዚህን ሕግጋት ብታዳምጥና በጥንቃቄ ብትጠብቃቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ከአንተ ጋር የገባውን የፍቅር ኪዳኑን ይጠብቃል።
13 ይወድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል።
14 ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም።
15 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብፅ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም።
16 አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።
17 “እነዚህ አሕዛብ ከእኛ ይልቅ ጠንካሮች ስለሆኑ፣ እንዴት አድርገን እናስወጣቸዋለን?” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል።