ዘፀአት 14:10-16 NASV

10 ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሃት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ።

11 እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን?

12 በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!”

13 ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም።

14 እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።

15 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤

16 ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ።