ዘፀአት 35 NASV

የሰንበት ሥርዐቶች

1 ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረሰብ ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤

2 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበት ዕረፍት፣ የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ በዕለቱ ማናቸውንም ዐይነት ሥራ የሚሠራ ቢኖር ሞት ይገባዋል።

3 በሰንበት ቀን በማናቸውም መኖሪያዎቻችሁ ውስጥ እሳት አታንድዱ።”

ለመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች

4 ሙሴ ለእስራኤላውያን ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤

5 ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ፣

6 ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣ የፍየል ጠጒር፣

7 ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ እንዲሁም አቆስጣ ቆዳ፣ የግራር ዕንጨት፤

8 ለመብራት የወይራ ዘይት፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን ቅመም፤

9 በኤፉዱና በደረት ኪሱ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎችን መባ አድርጎ ያምጣ።

10 “በመካከላችሁ ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ይሥሩ፤

11 የመገናኛውን ድንኳን ከነድንኳኑና ከነመደረቢያው፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤

12 ታቦቱን ከነመሎጊያዎቹ፣ የስርየት መክደኛውንና የሚሸፍነውን መጋረጃ፤

13 ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ዕቃዎቹን ሁሉና የሀልዎቱን ኅብስት፤

14 ለመብራት የሆነውን መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ ቀንዲሎችንና ለመብራት የሚሆነውን ዘይት፤

15 የዕጣን መሠዊያውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ቅብዐ ዘይቱንና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የሚሆነውን የመግቢያ መጋረጃ፤

16 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከናስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ የናስ ሰኑን ከነማስቀመጫው፣

17 ያደባባዩን መጋረጃዎች ከነምሶሶዎቻቸውና ከነመሠረቶቹ፣ ያደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፤

18 ለመገናኛው ድንኳንና ለአደባባዩ የሚሆኑ የድንኳን ካስማዎችና ገመዶቻቸው፤

19 በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይኸውም የካህኑ የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንዶች ልጆቹን ልብሶች ይሥሩ።”

20 ከዚያም የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤

21 ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አመጡ።

22 ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረቡ።

23 ሰማያዊ፣ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን ሐር ወይም የፍየል ጠጒር፣ ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ወይም የአቆስጣ ቆዳ አመጡ።

24 የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው።

25 ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ።

26 ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጒር ፈተሉ።

27 መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ።

28 እንዲሁም ለመብራቱ፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞችንና የወይራ ዘይትን አመጡ።

29 ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አመጡ።

ባስልኤልና ኤልያብ

30 ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጦአል።

31 በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቶበታል፤

32 ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤

33 ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።

34 እንዲሁም ለእርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው።

35 የጥበብ ባለ ሙያዎች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ በሰማያዊ በሐምራዊና በቀይ ማግ፣ በቀጭን ሐር ጥልፍ ጠላፊዎችና ፈታዮች፤ ሁሉም ዋና የጥበብ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጭዎች በመሆን ማንኛውንም ዐይነት ሥራ ያከናውኑ ዘንድ በጥበብ ሞል ቶአቸዋል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40