1 ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱ አምስት ክንድ የሆነ ባለ ዐራት ማእዘን ነበረ።
2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፣ መሠዊያውንም በናስ ለበጡት።
3 ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳህኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከናስ ሠሯቸው።
4 ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የናስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።
5 ለናሱ ፍርፍርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የናስ ቀለበቶችን ሠሩ።
6 መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በናስ ለበጧቸው።
7 መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።
8 የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የናስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።
9 ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤
10 ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የናስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት።
11 የሰሜኑም ክፍል ቁመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር፤ ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የናስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ነበሩት።
12 የምዕራቡ ጫፍ ወርዱ አምሳ ክንድ ነበር፤ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች እንዲሁም የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ያሉት መጋረጃዎች ነበሩት።
13 በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው የምሥራቁም ጫፍ ወርዱ አምሳ ክንድ ነበር።
14 ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋር ርዝመታቸው ዐሥራ አምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው መግቢያ ላይ ነበሩ፤
15 ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋር ርዝመታቸው ዐሥራ አምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአደባባዩ መግቢያ በሌላው በኩል ነበሩ።
16 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ ነበሩ።
17 የምሰሶዎቹ መቆሚያዎች ናስ ነበሩ፤ ኵላቦቹና በምሰሶዎቹ ላይ ያሉት ዘንጎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ ጫፎቻቸውም በብር ተለብጠው ነበር፤ ስለዚህ የአደባባዩ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሯቸው።
18 በአደባባዩ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና የጥልፍ ባለ ሙያ ከጠለፈው፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ ነበር፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፣ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች ከፍታው አምስት ክንድ ነበረ፤
19 አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ነበሩት፤ ኵላቦቻቸውና ዘንጎቻቸው የብር ሲሆኑ፣ ጫፎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር።
20 የማደሪያው ድንኳንና የአደባባዩ ዙሪያ ካስማዎች ሁሉ ከናስ የተሠሩ ነበሩ።
21 ለማደሪያው ድንኳን፣ ይኸውም ለምስክሩ ድንኳን ሙሴ ባዘዘው፣ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር መሪነት ሌዋውያኑ በጻፉት መሠረት የዕቃዎቹ ቍጥር ይህ ነው።
22 ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ የሆነው ባስልኤል፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
23 ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ፣ ዕቅድ አውጭና የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ጥልፍ ጠላፊ ነበር።
24 ለመቅደሱ ሥራ ሁሉ ከመወዝወዙ ስጦታ በመቅደሱ ሰቅል መሠረት የዋለው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።
25 በቈጠራው ወቅት ተቈጥረው ከነበሩት ማኅበረሰብ የተገኘው ብር ለመቅደሱ ሰቅል አንድ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅሎች ነበሩ፤
26 ከተቈጠሩት ጋር አብረው ከሆኑት ሃያና ከሃያ ዓመት በላይ የሆናቸው ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች የሰጡት እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በአንድ ሰው አንድ ቤካ ይኸውም ግማሽ ሰቅል ነበረ።
27 አንድ መቶ የብር መክሊቶች የመቅደሱንና የመጋረጃዎቹን መቆሚያዎች ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር፤ ይኸውም ከአንድ መቶ መክሊቶች አንድ መቶ መቆሚያዎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ መቆሚያ አንድ መክሊት ማለት ነው።
28 አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅሎችን ለምሰሶዎቹ ኵላቦች፣ የምሰሶዎቹን አናት ለመለበጥና ዘንጎቻቸውንም ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር።
29 ከመወዝወዙ ስጦታ የሆነው ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።
30 ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ለናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ ለዕቃዎቹም ሁሉ መቆሚያዎቹን ለመሥራት አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር፤
31 ለአደባባዩ ዙሪያ፣ ለመግቢያው እንዲሁም ለማደሪያው ድንኳን ካስማዎች ሁሉና ለአደባባዩ ዙሪያ ሁሉ እንዲሁ አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር።