ዘፀአት 27 NASV

የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረቢያ መሠዊያ

1 “ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ ርዝመቱ አምስት፣ ስፋቱም አምስት ክንድ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ይሁን።

2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፤ መሠዊያውንም በነሐስ ለብጠው።

3 ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የዐመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከነሐስ አብጃቸው።

4 ዐመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የነሐስ ፍርግርግ አድርግለት በአራቱም የመረብ ማእዘኖች ላይ የነሐስ ቀለበቶች አብጅ።

5 እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው።

6 የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው።

7 በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጎኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ።

8 መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፤ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሠረት ይበጅ።

የመገናኛው ድንኳን አደባባይ

9 “ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ አብጅለት፤ በደቡብ በኩል ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ይሁን፣ ከቀጭን በፍታ የተፈተሉ መጋረጃዎች፣

10 ሃያ ምሰሶዎች፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ይኑሩት።

11 በሰሜኑም በኩል አንድ መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይሁኑ፤ ሃያ ምሰሶዎቹ፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎችም ላይ ዘንጎች ይኑሩ።

12 “የአደባባዩ ምዕራብ ጫፍ ስፋቱ አምሳ ክንድ ሆኖ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች ያሉት መጋረጃዎች ይኑሩት።

13 በምሥራቅ ጫፍ በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው አደባባይ አሁንም አምስት ክንድ ስፋት ይኑረው።

14 ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት መቆሚያዎች ያሏቸው ርዝመታቸው ዐሥራ አምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው ደጃፍ ይሁኑ።

15 ሦስት ምሰሶዎች ሦስት መቆሚያዎች ያሏቸው ርዝመታቸው ዐሥራ አምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎች በሌላው በኩል ይሁኑ።

16 “ለአደባባዩ መግቢያ አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ያሉት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከቀጭን በፍታ የተፈተለ፣ ጥልፍ ጠላፊ የጠለፈበት ሃያ ክንድ ርዝመት ያለው መጋረጃ ይሁን።

17 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች፣ ኵላቦችና የነሐስ መቆሚያዎች ይኑሯቸው።

18 አደባባዩ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ፣ ስፋቱ አምሳ ክንድ ሆኖ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ማግ ቁመታቸው አምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎችና የነሐስም መቆሚያዎች ያሉት ይሁን።

19 ጥቅማቸው ምንም ዐይነት ይሁን፣ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች በሙሉ የድንኳኑና የአደባባዩ ካስማዎችም ሁሉ ሳይቀሩ ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ።

የመቅረዙ ዘይት

20 “መብራቶቹ ባለማቋረጥ እንዲበሩ ለመብራቱ የሚሆን ተወቅጦ የተጠለለ ንጹሕ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።

21 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው በስተውጭ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት፣ አሮንና ወንድ ልጆቹ መብራቶቹን ከምሽት እስከ ንጋት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንዲበሩ ያድርጉ፤ ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40