1 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤
2 “ከግብፅ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) እኔ ነኝ።”
3 “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።
4 “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ።
5 አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤
6 ነገር ግን ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።
7 “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የአምላክህን ስም ያለ አግባብ አታንሣ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።
8 “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብር።
9 ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን።
10 ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕለቱ አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ወይም ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በግቢህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም።
11 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፤ በሰባተኛው ቀን አርፎአልና። ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም።
12 ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።
13 “አትግደል።
14 “አታመንዝር።
15 “አትስረቅ።
16 “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17 “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።
18 “ሕዝቡም መብረቁንና ነጎድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤
19 ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዲናገረን አታድርግ፤ አለበለዚያ መሞታችን ነው” አሉት።
20 ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍርሃት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሊፈትናችሁ መጥቶአል” አላቸው።
21 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።
22 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤
23 ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ።
24 “ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በእርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ።
25 ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና።
26 ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል’።