ዘፀአት 16 NASV

መናና ድርጭት

1 መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብፅ በወጡ በሁለተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ከኤሊም ተነሥተው በኤሊምና በሲና መካከል ወደምትገኘው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ።

2 በምድረ በዳውም መላው ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ።

3 እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብፅ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው።

4 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰበስቡ፤ በዚህም ትእዛዛቴን ይጠብቁ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ።

5 በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።

6 ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብፅ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ።

7 በእርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጒረምረም ሰምቷልና በማለዳ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው።

8 ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጒረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው እንጂ” አላቸው።

9 ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጒረምረማችሁን እርሱ ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው።

10 አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር።

11 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

12 “የእስራኤላውያንን ማጒረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”

13 በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር።

14 ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ አመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ።

15 እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።ሙሴም፦ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጐሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዞአል።

17 እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።

18 የሰበሰቡትን በጐሞር በሰፈሩ ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አልጐደለበትም እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።

19 ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው።

20 ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግሥቱም ጠዋት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።

21 በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

22 ስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው እጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23 እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል። ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቆዩት።

24 ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቆዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

25 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም።

26 ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”

27 ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።

28 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እምቢ ትላላችሁ?

29 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቆይ፤ ማንም አይወጣም።”

30 ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።

31 የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።

32 ሙሴም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘን ይህ ነው፤ ‘ከግብፅ ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉ የሰጠኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ አንድ ጐሞር መና ወስደህ ለሚመጡት ትውልዶች አቆየው።’ ”

33 ስለዚህ ሙሴ አሮንን፣ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቆይም እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስቀምጠው” አለው።

34 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት አስቀመጠው።

35 እስራኤላውያን ወደ መኖሪያቸው ምድር እስኪመጡ ድረስ ለአርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ድንበር እስከሚደርሱ ድረስ መና በሉ።

36 አንድ ጎሞር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ነው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40