1 ለመቅደሱ አገልግሎት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ የተፈተሉ ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ።
2 ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ሠሩት፤
3 ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ይሠራ ዘንድ ወርቁን በስሱ ቀጥቅጠው እንደ ክር ቈራረጡት።
4 ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋር ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።
5 በጥበብ የተፈተለው መታጠቂያ በተመሳሳይ መልክ ሆኖ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከኤፉዱ ጋር አንድ ወጥ የሆነና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር የተሠራ ነበረ።
6 የከበሩ መረግዶችን በወርቅ ፈርጦች በመክፈፍ፣ እንደ ማኅተም የእስራኤልን ልጆች ስሞች ቀረጹባቸው።
7 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ላይ ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች አያያዟቸው።
8 የደረት ኪሱንም ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መንገድ ሠሩት፤ እንደ ኤፉዱም ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በቀጭኑም ከተፈተለ በፍታ ሠሩት።
9 ርዝመቱ አንድ ስንዝር ወርዱም አንድ ስንዝር ሲሆን፣ ጥንድ ድርብ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ነበረ።
10 ከዚያም የከበሩ ድንጋዮችን በአራት ረድፍ በላዩ ላይ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ነበር፤
11 በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና አልማዝ፣
12 በሦስተኛውም ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፣
13 በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጲድ ነበረ፤ በወርቅ ፈርጥ ላይ ተደርገው ነበር።
14 ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም አንዳንድ ሆኖ፣ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ማኅተም ከዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የአንዱ ስም የተቀረጸበት ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ነበሩ።
15 ለደረት ኪሱም ልክ እንደ ገመድ ከንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አበጁለት።
16 ሁለት የወርቅ ፈርጦችንና ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ቀለበቶቹን ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋር አያያዟቸው።
17 ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረት ኪሱ ጐንና ጐን ካሉት ቀለበቶች ጋር አያያዟቸው፤
18 የድሪዎቹን ሌሎች ጫፎች ከፊት ካለው ከኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ጋር በማገናኘት ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋር አያያዟቸው።
19 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ከኤፉዱ ቀጥሎ ካሉት ከሌሎቹ ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋር ከውስጠኛው ጠርዝ ላይ አያያዟቸው።
20 ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ልክ ከኤፉዱ መታጠቂያ በላይ፣ ከመጋጠሚያው አጠገብ፣ ከኤፉዱ ፊት ለፊት ካሉት ከትከሻ ንጣዮች ጋር አያያዟቸው።
21 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ተነጥሎ ለብቻው እንዳይንጠለጠል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከመታጠቂያው ጋር በማገናኘት፣ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሠሯቸው።
22 የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ሠሩት፤
23 ይህም እንደ ክሳዱ ቅድ ከቀሚሱ መካከል ላይ አንገትጌ ነበረው፤ እንዳይተረተርም በአንገትጌው ዙሪያ ላይ ቅምቅማት ነበረው።
24 በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ላይ ሮማኖቹን አደረጉ።
25 ከንጹሕ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ እነዚህንም በሮማኖቹ መካከል በጠርዙ ዙሪያ አደረጉ።
26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአገልግሎት ይለበሱ ዘንድ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ላይ ተሰባጥረው ይገኙ ነበር።
27 ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የሸማኔ ሥራ የሆነውን ከቀጭን በፍታ ሸሚዞችን ሠሩ፤
28 እንዲሁም ከቀጭን በፍታ ጥምጥምን፣ የሐር ቆቦቹንና በቀጭኑ ከተፈተለም በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ።
29 መታጠቂያው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ የጥልፍ ጠላፊ ሥራ ሆኖ የተሠራ ነበረ።
30 ከንጹሕ ወርቅ የተቀደሰውን አክሊል ሰሌዳ ሠርተው፣ በማኅተም ላይ እንደ ተቀረጸ ጽሑፍ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)” የሚል ቀረጹበት፤
31 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ከመጠምጠሚያው ጋር ለማያያዝ ሰማያዊ ፈትል አሠሩበት።
32 በዚህ መሠረት የማደሪያው ድንኳን፣ የመገናኛው ድንኳን ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉን ነገር ሠሩ።
33 ከዚያም የማደሪያውን ድንኳን ወደ ሙሴ አመጡት፤ እነዚህም ድንኳንና ዕቃዎቹ ሁሉ፣ ማያያዣዎቹ፣ ክፈፎቹ፣ አግዳሚዎቹ፣ ምሰሶዎቹና መቆሚያዎቹ፤
34 ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ የተሠራ መደረቢያ፣ የለፋ የአቆስጣ ቆዳ መደረቢያና መከለያ መጋረጃ፤
35 የምስክሩ ታቦት፣ ከመሎጊያዎቹና ከስርየት መክደኛው ጋር፤
36 ጠረጴዛው ከዕቃዎቹ ሁሉና ከኅብስተ ገጹ ጋር፤
37 ከንጹሕ ወርቅ የሆነው መቅረዝ ከተደረደሩት መብራቶችና ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር፣ የመብራቱም ዘይት፣
38 የወርቅ መሠዊያው፣ ቅብዐ ዘይቱ፣ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን እንዲሁም የድንኳኑ መግቢያ መጋረጃ፣
39 የናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ ሁሉ ጋር፤ የመታጠቢያው ሳሕን ከነማስቀመጫው፣
40 የአደባባዩ መጋረጃዎች ከምሰሶዎቹና ከመቆሚያዎቹ ጋር፣ የአደባባዩ መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹና የአደባባዩ ድንኳን ካስማዎች፣ የማደሪያው የመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ፤
41 በመቅደሱ ሲያገለግሉ የሚለበሱት የተፈተሉት ቀሚሶች፣ ለካህኑ ለአሮን የተቀደሱት ቀሚሶችና ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚያደርጓቸው ቀሚሶች ናቸው።
42 እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ሥራውን ሁሉ አከናወኑ።
43 ሙሴ ሥራውን አየ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው መሥራታቸውንም ተመለከተ፤ ስለዚህ ባረካቸው።