ዘፀአት 3:1-7 NASV

1 አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የአማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ።

2 እዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለ መቃጠሉን አየ።

3 ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ።

4 ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው፤ ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው።

5 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ስለሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው

6 ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።

7 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ እንዲህ አለ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።