ዘፀአት 32:4-10 NASV

4 እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ።

5 አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ።

6 በማግሥቱ ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።

7 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣኻቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ አለው፤

8 ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ።

9 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ አንገተ ደንዳናዎችም ናቸው፤

10 አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”