1 ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱ አምስት ክንድ የሆነ ባለ ዐራት ማእዘን ነበረ።
2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፣ መሠዊያውንም በናስ ለበጡት።
3 ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳህኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከናስ ሠሯቸው።
4 ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የናስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።
5 ለናሱ ፍርፍርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የናስ ቀለበቶችን ሠሩ።