9 እነዚህ አምስቱ፣ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፣ በጎይም ንጉሥ በቲድዓል፣ በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፣ በእላሳር ንጉሥ በኦርዩክ፣ በእነዚህ በአራቱ ላይ ዘመቱባቸው።
10 በሲዲም ሸለቆ ብዙ የቅጥራን ጒድጓዶች ስለ ነበሩ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሲሸሹ ከሰዎቻቸው አንዳንዶቹ በነዚህ ጒድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራሮች ሸሹ።
11 አራቱ ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ሀብትና ምግብ ሁሉ ዘርፈው ሄዱ።
12 የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ።
13 ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ አስኮና አውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ።
14 አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ።
15 አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው።