1 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ነገሠ፤
2 በኢየሩሳሌም ሆኖ ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።
3 እርሱም አባቱ ከእርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም።
4 ነገር ግን ከእርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው።
5 ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።
6 አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።
7 ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።