1 ነገሥት 22 NASV

ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ

1 በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም።

2 በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ።

3 የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።

4 ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት ላይ ለመዝመት አብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው።ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ ያው እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለ።

5 ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

6 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ልዝመት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

7 ኢዮሣፍጥ ግን፣ “የምንጠይቀው የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

8 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ አንዳችም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።

9 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “በል የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።

10 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር አጠገብ ባለው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ሳለ፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

11 በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።

12 የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።

13 ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና ያንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው።

14 ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።

15 እዚያም እንደ ደረሰ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ እንዝመትባት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዘምተህ ድል አድርጋት” ብሎ መለሰለት።

16 ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

17 ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።”

18 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

19 ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ስማ፤ ‘እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይ ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ፤

20 እግዚአብሔርም፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት፣ አክዓብን ማን ያስተው?” አለ።’“ታዲያ አንዱ ይህን፣ ሌላውምያን አለ፤

21 በመጨረሻም፣ ‘አንድ መንፈስ ወጣ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፣ “እኔ አስተዋለሁ” አለ።’

22 እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣለሁ፤ በገዛ ነቢያቱም አፍ ሁሉ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም፣ “በል እንግዲያው ውጣና አስተው፤ ይሳካልሃል” አለው።

23 “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ በአንተም ላይ መዓቱን እንደሚያመጣብህ ተናገረ።”

24 ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ በየት በኩል ዐልፎ ነው አንተን መጥቶ ያናገረህ?” ሲል ጠየቀው።

25 ሚክያስም፤ “ይህንማ ለመደበቅ ወደ አንዲት እልፍኝ በሄድህ ዕለት ታውቀዋለህ” አለው።

26 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “በሉ ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤

27 ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ “በደኅና እስክመለስ ድረስ፣ ይህን ሰው በእስር ቤት አቈዩት፤ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በስተቀር ሌላ እንዳትሰጡት” ብሎአል በሉት’ አለ።

28 ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስህ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረማ!” አለ፤ ከዚያም በመቀጠል፣ “በዚህ ያለኸው ሕዝብ ሁሉ ይህን ቃሌን ልብ ብለህ ያዘው፤” አለ።

አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው በሬማት ተገደለ

29 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ወደምትገኘው ሬማት ወጡ።

30 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እንዳልታወቅ እኔ ልብስ ለውጬና ሌላ ሰው መስዬ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ራሱን ደብቆ ወደ ጦርነቱ ገባ።

31 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ይሁን ትልቅ ከማንም ጋር እንዳትገጥሙ” ሲል አዞአቸው ነበር፤

32 የሠረገላ አዛዦቹ ኢዮሣፍጥን ሲያዩት፣ “ያለ ጥርጥር ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ስለዚህ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ሲጮህ ግን

33 የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን አውቀው መከታተሉን ተዉት።

34 ነገር ግን አንዱ ቀስቱን ሳያልም እንዲሁ ሲያስፈነጥር በጦር ልብሱ መጋጠሚያ ላይ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው፤ ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን፣ “ቈስያለሁና ወደ ኋላ አዙረህ ከጦሩ ሜዳ አውጣኝ” አለው።

35 ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜም ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት ሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቊስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያኑ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ።

36 ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ።

37 ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ።

38 ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ ኵሬ አጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት።

39 ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝሆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

40 አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ

41 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ።

42 ኢዮሣፍጥ ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱ ዓዙባ ትባላለች፤ እርሷም የሺልሒ ልጅ ነበረች።

43 በአካሄዱም ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያች ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ፣ ዕጣንም ያጥን ነበር።

44 እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር በሰላም ኖረ።

45 ሌላውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ የፈጸመው፣ ያከናወነውና ያደረገው ጦርነት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

46 ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ።

47 በዚያን ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።

48 ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የንግድ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር።

49 በዚያን ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን እሺ አላለውም።

50 ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ

51 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ።

52 እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ።

53 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ እንዲነሣሣ አደረገ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22