1 ነገሥት
ምዕራፎች 16
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤
2“ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቊጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው።
3ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ።
4በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።”
5በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
6ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
7ከዚህም በቀር የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤቱ ላይ የመጣበት ምክንያት፣ በእጁ ሥራ ያስቈጣው ዘንድ እንደ ኢዮርብዓም ቤት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሁሉ በማድረጉና ኢዮርብዓምን በማጥፋቱም ጭምር ነው።