1 ነገሥት 15 NASV

የይሁዳ ንጉሥ አብያ

1 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ነገሠ፤

2 በኢየሩሳሌም ሆኖ ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

3 እርሱም አባቱ ከእርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

4 ነገር ግን ከእርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው።

5 ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።

6 አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።

7 ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።

8 አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሳ

9 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤

10 በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ አያቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

11 አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።

12 የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ።

13 አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።

14 አሳ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር።

15 አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

16 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

17 የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።

18 አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በታማኝ ሹማምቱ እጅ በደማስቆ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሀዳድ ላከው።

19 እንዲህም አለ፤ “በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ አሁንም በእኔና በአንተ መካከል ይኑር፤ እነሆ፣ የብርና የወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ወደ መጣበት እንዲመለስ፣ ሄደህ ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ።”

20 ቤንሀዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ጌንሳሬጥን በሙሉ ድል አደረገ።

21 ባኦስም ይህን ሲሰማ፣ በራማ የጀመረውን የምሽግ ሥራ አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ።

22 ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ አስቀምጦት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ ንጉሡም በዚሁ ምጽጳንና በብንያም ውስጥ ጌባን ሠራ።

23 በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፈው የሚገኙ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹ ታመሙ።

24 አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ

25 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ ዘመነ መንግሥት በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

26 እርሱም በአባቱ መንገድ በመሄድ፣ አባቱ የሠራውንና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመሥራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

27 ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው።

28 ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው።

29 ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤

30 ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ በማነሣሣቱ ነው።

31 ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

32 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ

33 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ።

34 በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22