1 ነገሥት 3 NASV

ሰሎሞን ጥበብን ከእግዚአብሔር መለመኑ

1 ሰሎሞን የግብፅ ንጉሥ የፈርዖን ወዳጅ ሆነ፤ የፈርዖንንም ልጅ አገባ። እርሱም ቤተ መንግሥቱን፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጥር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አስቀመጣት።

2 በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ስም ገና ቤተ መቅደስ ስላልተሠራ፣ ሕዝቡ አሁንም መሥዋዕት የሚያቀርበው በማምለኪያ ኰረብታ ላይ ነበር።

3 ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ በአባቱ በዳዊት ሥርዐትም ይሄድ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ በኰረብታዎች ላይ መሥዋዕት ይሠዋና ዕጣን ያጥን ነበር።

4 ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

5 በገባዖንም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን” አለው።

6 ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ ዳዊት በእውነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኸዋል።

7 “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም።

8 ባሪያህ አንተ በመረጥኸው ሕዝብ፣ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል።

9 ስለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”

10 ሰሎሞን ይህን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፤

11 ስለዚህ እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ፣ ብልጽግና እንድታገኝ ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ ሳይሆን፣ በትክክል ማስተዳደር እንድትችል ማስተዋልን ስለ ጠየቅህ፣

12 ይህንኑ አደርግልሃለሁ፤ ከአንተ በፊት ማንም ያልነበረውን፣ ከአንተም በኋላ ማንም የማያገኘውን ጥበብና አስተዋይ ልቡና እሰጥሃለሁ፤

13 ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅኸውን ብልጽግናና ክብር እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በሕይወት ዘመንህ የሚተካከልህ ማንም ንጉሥ እንዳይኖር ነው።

14 አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።”

15 ሰሎሞንም ከእንቅልፉ ነቃ፤ እነሆ ሕልም መሆኑን ተረዳ።ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ፣ በጌታ ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብዣ አደረገ።

ጥበብን የተሞላ ፍትሕ

16 በዚህን ጊዜ ሁለት ዝሙት አዳሪዎች ወደ ንጉሡ መጥተው ከፊቱ ቆሙ።

17 ከእነርሱም አንዲቱ እንዲህ አለች፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን እንኖራለን፤ አብራኝ እያለችም እኔ ልጅ ወለድሁ፤

18 እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላም፣ ይህች ሴት ወለደች፤ ያለ ነው እኛ ብቻ ነን፤ ከሁለታችን በቀር በዚያ ቤት ማንም አልነበረም።

19 “የዚህች ሴት ሕፃን ልጅ ስለ ተኛችበት ሌሊት ሞተ።

20 ስለዚህም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፣ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደችው፤ ከዚያም የእኔን ልጅ ራሷ ታቅፋ፣ የሞተ ልጇን አምጥታ በዕቅፌ አደረገችው።

21 በማግሥቱ ልጄን ላጠባ ስነሣ እነሆ ሞቶአል፤ ነገር ግን በማለዳ ብርሃን ትክ ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድሁት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብሁ።

22 ሌላዪቱም ሴት፣ “ነገሩ አንቺ እንደ ምትዪው አይደለም፤ የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለውም የእኔ ነው” አለች።የመጀመሪያዋ ሴት ግን አጠንክራ፣ “አይደለም! የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው” አለች፤ በዚህ ሁኔታም በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።

23 ንጉሡም፣ “ይህችኛዪቱ፣ ‘የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው፣ የአንቺ የሞተው ነው’ ትላለች፤ ያችኛዪቱ ደግሞ፣ ‘አይደለም የአንቺ ልጅ ሞቶአል፣ በሕይወት ያለው የእኔ ነው’ ትላለች” አለ።

24 ከዚያም ንጉሡ፣ “እንግዲያውስ ሰይፍ አምጡልኝ” አለ፤ ለንጉሡም ሰይፍ አመጡለት።

25 በዚህ ጊዜ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ልጅ ከሁለት ክፈሉና ለአንዷ ግማሹን፣ ለሌላዪቱም ግማሹን ስጡ” ብሎ አዘዘ።

26 በሕይወት ያለው ልጅ እናት ለልጇ እጅግ ስለ ራራች ንጉሡን፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለእርሷ ስጣት፤ አትግደለው” አለች።ሌላዪቱ ግን፣ “ለእኔም ሆነ ለአንቺ አይሰጥም፤ ሁለት ላይ ይከፈል!” አለች።

27 ከዚህ በኋላ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለመጀመሪያዪቱ ሴት ስጧት፤ አትግደሉት፤ እናቱ እርሷ ናት” አለ።

28 እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ የሰጠውን ፍርድ ሲሰሙ ፈሩት፤ ፍትሕ ለመስጠት የአምላክን ጥበብ የታደለ መሆኑን አይተዋልና።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22