15 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከቦ ሰፍሮ ነበር።
16 በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያኑ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ።
17 ከዚያም ዖምሪና አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።
18 ዘምሪ ከተማዪቱ መያዟን ሲያይ፣ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ግንብ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበትና በዚሁ ሞተ።
19 ይህ የሆነውም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ በመሥራትና በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድ፣ እንዲሁም ራሱ በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ምክንያት ነው።
20 ሌላው ዘምሪ በዘመኑ የፈጸመው ድርጊትና ያካሄደውም ዐመፅ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አደለምን?
21 ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፣ ይህም ግማሹ የጎናትን ልጅ ታምኒን ለማንገሥ ሲሆን፣ የቀረው ደግሞ ዖምሪን በመደገፍ ነበር።