31 “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ መማል ኖሮበት ቢመጣና በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣
32 ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት።
33 ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣
34 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህ የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሰህ አግባቸው።
35 “ሕዝቡም አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከበደላቸው ቢመለሱ፣
36 በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ ለሰጠሃትም ምድር ዝናብ አውርድ።
37 “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት፣ ዋግ ወይም አረማሞ በሚከሠትበት፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚወርድበት ወይም በምድራቸው ውስጥ ባሉት ከተሞቻቸው ጠላት ቢከባቸው እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚመጣባቸው ጊዜ፣