2 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንደ አደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ።
4 በየኰረብታው ላይ ያሉት ማምለኪያዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በየኰረብታው ላይ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
5 አሜስያስ መንግሥቱን አጽንቶ ከያዘ በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው፤
6 ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር፣ “እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል እንጂ አባቶች በልጆቻቸው፣ ልጆችም በአባቶቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም።
7 የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺህ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው።
8 ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት ይዋጣልን” ሲል መልእክተኞች ላከበት።