2 ነገሥት 8 NASV

የሱነማዪቱ ርስት ተመለሰ

1 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተሰብሽ ጋር ሂጂ” አላት።

2 ሴቲቱም ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገራት አደረገች፤ ከነቤተ ሰቧም ሄዳ፣ በፍልስጥኤም ምድር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።

3 ከሰባት ዓመት በኋላም፣ ከፍልስጥኤም ምድር ተመልሳ መጣች፤ ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ አቤቱታ ለማቅረብ፣ ወደ ንጉሡ ሄደች።

4 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስቲ ንገረኝ” እያለው ነበር።

5 ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ፣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር።ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ።

6 ንጉሡም ስለ ዚሁ ጒዳይ ጠየቃትና ነገረችው።ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።

አዛሄል ቤንሃዳድን ገደለ

7 ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ታሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።

8 እርሱም አዛሄልን፣ “ገጸ በረከት ይዘህ ሂድና የእግዚአብሔርን ሰው ተገናኘው። በእርሱም አማካይነት፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው።

9 አዛሄልም ደማስቆ ካፈራቻቸው ምርጥ ነገሮች ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ይዞ ኤልሳዕን ለመገናኘት ሄደ። ሄዶም እፊቱ ቆመና፣ “የሶርያ ንጉሥ ልጅህ ቤን ሃዳድ፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።

10 ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት።

11 እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።

12 አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጒዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጐልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።

13 አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።

14 ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤንሀዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው።

15 በማግስቱ ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሆራም

16 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮሆራም በይሁዳ ነገሠ።

17 እርሱም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

18 ያገባት የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

19 ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ለዳዊትና ለዘሩ መብራት እንደማያሳጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

20 በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

21 ስለዚህም ኢዮሆራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ከበቡ፤ እርሱና የሠረገላ አዛዦቹ ግን በሌሊት ተነሥተው ከበባውን ጥሰው ወጡ፤ ሰራዊቱም ሸሽቶ ተመለሰ።

22 ኤዶምያስም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር።

23 በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

24 ኢዮሆራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ

25 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ በይሁዳ ነገሠ።

26 አካዝያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሀያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ጎቶልያ ትባላለች፤ እርሷም የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች።

27 አካዝያስ ከአክዓብ ቤተ ሰብ ጋር በጋብቻ የተሳሰረ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

28 አካዝያስም ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ በሶርያ ንጉሥ በአዛሄል ላይ ለመዝመት ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ፤ ሶርያውያንም በዚያ ኢዮራምን አቈሰሉት።

29 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፣ በሬማት ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሶርያውያን ካደረሱበት ቊስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።ከዚያም የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ስለ ታመመ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራሆም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25