16 በተጨማሪም፣ ስማቸው በትውልድ መዝገቡ ውስጥ የነበረና የየዕለቱ ልዩ ልዩ ተግባራቸውን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው ለማከናወን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት ለሚችሉት፣ ዕድሜአቸው ሦስት ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ወንዶች ልጆች እንደዚሁ አከፋፈሉ።
17 በትውልድ መዝገብ በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ለገቡት ካህናት፣ ዕድሜአቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆናቸው ሌዋውያን እንደየኀላፊነታቸው መጠንና እንደየምድብ ሥራቸው አካፈሏቸው።
18 በዚህ የትውልድ መዝገብ ላይ የተዘረዘሩትን መላውን የማኅበረሰቡን ሕፃናት፣ ሚስቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጨመሯቸው፤ ራሳቸውን በመቀደስ ታማኞች ነበሩና።
19 በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉት የዕርሻ ቦታዎች፣ ወይም በሌሎች ከተሞች ሁሉ ለሚኖሩት ለካህናቱ ለአሮን ዘሮች፣ በመካከላቸው ላሉት ወንዶችና በሌዋውያን የትውልድ መዝገብ ለተመዘገቡት ሁሉ እንዲያከፋፍሉ በየስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20 ሕዝቅያስ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካም፣ ቅንና ታማኝ ሆኖ በመገኘት በመላው ይሁዳ የፈጸመው ተግባር ይህ ነው።
21 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማገልገልም ሆነ፣ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ በመገዛት አንጻር ያደረገውን ሁሉ በፍጹም ልቡ አምላኩን በመፈለግ አከናወነ፤ ተሳካለትም።