1 ነገሥት 1:15-21 NASV

15 ስለዚህ ቤርሳቤህ፣ ሱነማዊቷ አቢሳ በምታገለግልበት ክፍል እርጅና የተጫጫነውን ንጉሥ ለማነጋገር ሄደች።

16 ቤርሳቤህም ለጥ ብላ እጅ ከነሣች በኋላ እፊቱ በጒልበቷ ተንበረከከች።ንጉሡም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

17 እርሷም እንዲህ አለችው፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ ቀጥሎ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ አንተው ራስህ ለአገልጋይህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኝ ነበር።

18 እነሆ፤ አሁንም አዶንያስ ነግሦአል፤ ንጉሥ ጌታዬ አንተ ግን ስለዚህ ነገር አታውቅም።

19 እርሱ በሬዎችን፣ ኮርማዎችንና በጎችን በብዛት ሠውቶአል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሰራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም።

20 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ከአንተ ቀጥሎ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ ማን መቀመጥ እንዳለበት እንድታሳውቀው የእስራኤል ዐይን ሁሉ አንተን ይመለከታል።

21 ያለበለዚያ ግን ንጉሥ ጌታዬ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ወንጀለኞች እንቈጠራለን።”