1 ነገሥት
ምዕራፎች 1:38-44
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
38ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወርደው ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ አስቀምጠው በማጀብ ወደ ግዮን አመጡት።
39ካህኑ ሳዶቅም የዘይቱን ቀንድ ከመገናኛው ድንኳን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው፤ ከዚያም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ሕዝቡም በሙሉ፣ “ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!” በማለት ዳር እስከ ዳር አስተጋቡ።
40ሕዝቡ ሁሉ እንቢልታ እየነፋና እጅግ እየተደሰተ አጀበው፤ ከድምፁ የተነሣም ምድሪቱ ተናወጠች።
41አዶንያስና የተጠሩት እንግዶች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ፣ ይህንኑ ሰሙ፤ ኢዮአብም የመለከቱን ድምፅ ሲሰማ፣ “ይህ በከተማዪቱ ውስጥ የሚሰማው ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
42ኢዮአብ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ደረሰ፤ አዶንያስም፣ “እንዳንተ ያለ ታማኝ ሰው መልካም ዜና ሳይዝ አይመጣምና ግባ” አለው።
43ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ነገሩ ከቶ እንዲህ አይደለም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል።
44ንጉሡ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን አብረውት እንዲሄዱ አድርጎአል፤ እነርሱም በንጉሡ በቅሎ አስቀመጡት።