1 ነገሥት 10:1-7 NASV

1 ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ዝና እና ከእግዚአብሔር ስም ጋር ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች።

2 ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቶ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ዕንቆች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት።

3 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ንጉሡ አቅቶት የቀረ አንዳች ጥያቄ አልነበረም።

4 ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት

5 እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አሳላፊዎቹን ከነደንብ ልብሳቸው፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ስታይ እጅግ ተደነቀች።

6 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስላከናወንኸው ሥራና ስለ ጥበብህ ባገሬ ሳለሁ የሰማሁት ትክክል ነው፤

7 ይሁን እንጂ፣ ራሴ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በእርግጥ ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት በላይ ነው።