1 ነገሥት 10:15-21 NASV

15 ይህም ከንግድና ከሌላ ገቢ ላይ የሚከፈለውን ቀረጥ፣ የዐረብ ነገሥታት ሁሉ የሚያገቡትንና አገረ ገዦች የሚሰበስቡትን ግብር ሳይጨምር ነው።

16 ንጉሥ ሰሎሞን ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ሦስት መቶ ሰቅል ወርቅ ነበር።

17 እንዲሁም ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ደግሞ ሦስት ምናን ወርቅ ነው። ንጉሡም እነዚህን የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት አኖረ።

18 ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው።

19 ዙፋኑ ባለ ስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል።

20 በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም።

21 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም።