13 ይህም ሆኖ መንግሥቱን በሙሉ አልነጥቀውም፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”
14 እግዚአብሔር ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተ ሰብ ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰሎሞን ላይ አስነሣው።
15 ከዚያ በፊት ዳዊት ከኤዶም ጋር በተዋጋ ጊዜ፣ የሞቱትን ለመቅበር መጥቶ የነበረው የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብ የኤዶምን ሰዎች ሁሉ ፈጅቶ ነበር።
16 ኢዮአብና እስራኤላውያን ሁሉ፣ በኤዶም ያሉትን ወንዶች በሙሉ እስኪያጠፉ ድረስ፣ እዚያው ስድስት ወር ቈይተው ነበርና።
17 ሃዳድ ግን ገና በልጅነቱ አባቱን ካገለገሉ ጥቂት ኤዶማውያን ጋር ወደ ግብፅ ሸሸ፤
18 እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከፋራንም ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ በመምጣት፣ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገቡ። ንጉሡም ለሃዳድ ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም አዘዘለት።
19 ፈርዖንም ሃዳድን እጅግ ወደደው፤ ስለዚህም ከሚስቱ ከንግሥት ጣፍኔስ እኅት ጋር አጋባው።