1 ነገሥት 11:26-32 NASV

26 እንዲሁም ከሰሎሞን ሹማምት አንዱ የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እርሱም ከጸሬዳ የመጣ ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ እናቱ ጽሩዓ የተባለች መበለት ነበረች።

27 በንጉሡ ላይ ያመፀበትም ምክንያት እንዲህ ነው፤ ሰሎሞን ድጋፍ የሚሆኑ እርከኖች በመሥራት የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ይጠግን ነበር።

28 ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ሰሎሞንም ወጣቱ ሥራውን እንዴት በሚገባ እንደሚያከናውን ባየ ጊዜ፣ በዮሴፍ ነገድ ለሚሠራው የጒልበት ሥራ ሁሉ ኀላፊ አደረገው።

29 በዚያ ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ የሴሎው ነቢይ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ መጐናጸፊያ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱ ብቻቸውን ሳሉ፣

30 አኪያ የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ ይዞ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቀደደው።

31 ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ መንግሥቱን ከሰሎሞን እጅ እቀዳለሁ፤ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጣለሁ፤

32 ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንድ ነገድ ይቀርለታል፤