1 ነገሥት 11:33-39 NASV

33 ይህን የማደርገውም እኔን ትተው የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፣ የሞዓብን አምላክ ካሞሽን፣ የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ስላመለኩ እንዲሁም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ስላልሄዱ በፊቴ ትክክለኛውን ነገር ስላላደረጉ፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ስላልጠበቁ ነው።

34 “ ‘ይሁን እንጂ መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድበትም፤ ስለ መረጥሁት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲገዛ አድርጌዋለሁ።

35 መንግሥትን ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ።

36 ስሜ እንዲኖርባት በመረጥኋት በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ ለባሪያዬ ለዳዊት ምንጊዜም በፊቴ መብራት እንዲኖረው፣ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጣለሁ።

37 አንተን ግን እኔ እወስድሃለሁ፤ ልብህ በወደደው ሁሉ ላይ ትነግሣለህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ትሆናለህ።

38 ባሪያዬ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን በመጠበቅ ትክክል የሆነውን ነገር በፊቴ ብታደርግ፣ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት እንዳጸናሁ፣ ለአንተም አጸናልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጣለሁ።

39 ከዚህ የተነሣም የዳዊትን ቤት አዋርዳለሁ፤ ነገር ግን ለዘላለም አይደለም።’ ”