1 ነገሥት 11:7-13 NASV

7 ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራ ላይ ለአስጸያፊው የሞዓብ አምላክ ለካሞሽ እንዲሁም አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ማምለኪያ ኰረብታ ሠራ።

8 ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑና መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ለሌሎቹ ሚስቶቹም ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሠራላቸው።

9 ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡ ስለሸፈተ፣ እግዚአብሔር ተቈጣው።

10 ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፣ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤

11 ስለዚህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ይህን በማድረግህ ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤

12 ይህን ግን ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በዘመንህ አላደርገውም፤ መንግሥትህን የምቀዳት ከልጅህ እጅ ነው።

13 ይህም ሆኖ መንግሥቱን በሙሉ አልነጥቀውም፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”