1 ነገሥት 13:16-22 NASV

16 የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህ ቦታም አብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤

17 ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው።

18 ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።

19 ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።

20 በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤

21 ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤

22 ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።