1 ነገሥት 14:13-19 NASV

13 እስራኤልም ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ በወግ በማዕረግ የሚቀበር እርሱ ብቻ ነው።

14 “ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ የሚያስወግድ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ለራሱ ያስነሣል፤ ይህም ዛሬ፣ አሁኑኑ ይሆናል።

15 እግዚአብሔር እስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድ በመሥራት እግዚአብሔርን ለቊጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።

16 ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋቸዋል።

17 የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤

18 ከዚያም ቀበሩት፤ እግዚአብሔር በባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።

19 የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።