1 ነገሥት 16:11-17 NASV

11 ዘምሪ ወዲያው እንደ ነገሠና በዙፋን እንደ ተቀመጠ፣ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፤ የሥጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አንድም ወንድ አላስቀረም።

12 በዚህ ሁኔታም በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የባኦስን ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጀ።

13 ይህም የሆነው ባኦስና ልጁ ኤላ፣ በማይረቡ ጣዖቶቻቸው ምክንያት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ በሠሩት ኀጢአት ሁሉና፣ እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ነበር።

14 ሌላው ኤላ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

15 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከቦ ሰፍሮ ነበር።

16 በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያኑ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ።

17 ከዚያም ዖምሪና አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።