1 ነገሥት 16:28-34 NASV

28 ዖምሪ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

29 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የዖምሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፣ በሰማርያም ሆኖ እስራኤልን ሃያ ሁለት ዓመት ገዛ።

30 የዖምሪ ልጅ አክዓብ ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

31 የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት እንደ ቀላል ነገር ከመቍጠሩም በላይ የሲዶናውያንን ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፤ ሄዶም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም።

32 ሰማርያ ላይ በሠራውም የበኣል ቤተ ጣዖት ለበኣል መሠዊያ አቆመለት።

33 ደግሞም አክዓብ የአሼራን ምስል ዐምድ በማቆም ከእርሱ በፊት ከነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ የሚያነሣሣ ድርጊት ፈጸመ።

34 የቤቴል ሰው አኪኤል፣ በአክዓብ ዘመን ኢያሪኮን መልሶ ሠራት። እግዚአብሔር በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካይነት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ መሠረቷን ሲያኖር በኵር ልጁ አቢሮን ሞተ፤ የቅጽር በሮቿንም በሚሠራበት ጊዜ የመጨረሻው ልጁ ሠጉብ ሞተ።