1 አክዓብ በዚህ ጊዜ፣ ኤልያስ ያደረገውን በሙሉ፣ ነቢያቱንም ሁሉ እንዴት በሰይፍ እንዳስገደላቸው ለኤልዛቤል ነገራት።
2 ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
3 ኤልያስም ፈርቶ ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤
4 በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ።
5 ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው።በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።
6 ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ እንጎቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።