1 ነገሥት 19:3-9 NASV

3 ኤልያስም ፈርቶ ስለ ነበር፣ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ሸሸ። በይሁዳ ምድር ወዳለችው ወደ ቤርሳቤህ እንደ መጣም አገልጋዩን በዚያ ተወው፤

4 በምድረ በዳም ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ ወደ አንድ ክትክታ ዛፍ እንደ መጣም፣ ከሥሩ ተቀምጦ፣ ይሞት ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” ብሎ ጸለየ።

5 ከዚያም ከዛፍ ሥር ተጋደመ፤ እንቅልፍም ወሰደው።በድንገትም አንድ መልአክ ነካ አደረገውና፣ “ተነሥና ብላ” አለው።

6 ዘወር ብሎ ሲመለከትም፣ እነሆ፣ በፍም የተጋገረ እንጎቻና አንድ ገንቦ ውሃ ከራስጌው አገኘ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ።

7 የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው።

8 ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤

9 በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው።