1 ነገሥት 2:17-23 NASV

17 እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እምቢ አይልሽምና ሱነማዊቷን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት።

18 ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች።

19 ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጒዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።

20 እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ እሺ በለኝ” አለችው።ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት።

21 ስለዚህም፣ “ሱነማዊቷን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው።

22 ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዊቷን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለ ሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት።

23 ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤