1 ነገሥት 20:32-38 NASV

32 እነርሱም በወገባቸው ላይ ማቅ ታጥቀው፣ በራሳቸው ላይ ገመድ ጠምጥመው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመሄድ፣ “አገልጋይህ ቤን ሀዳድ፣ ‘እባክህ በሕይወት እንድኖር ፍቀድልኝ’ ብሎ ይለምንሃል” አሉት።ንጉሡም፣ “እስካሁን በሕይወት አለን? ወንድሜ እኮ ነው” አለ።

33 ሰዎቹም ይህን በደግ በመተርጐም ቃሉን ከአፉ ቀበል አድርገው፤ “አዎን ቤን ሀዳድ ወንድምህ ነው” አሉት።ንጉሡም፣ “በሉ ሂዱና አምጡት” አላቸው፤ ቤንሀዳድም በመጣ ጊዜ፣ አክዓብ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።

34 ቤንሀዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው።አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው።

35 ከነቢያት ልጆች አንዱ ጓደኛውን በእግዚአብሔር ቃል ታዞ፣ “ምታኝ” አለው፤ ሰውየው ግን ፈቃደኛ አልሆነም።

36 ስለዚህም ነቢዩ፣ “ለእግዚአብሔር ባለ መታዘዝህ፣ ከእኔ ተለይተህ እንደሄድህ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ሰውየው ከሄደ በኋላ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።

37 ነቢዩም ሌላ ሰው አግኝቶ፣ “እባክህ ምታኝ” አለው። ስለዚህ ያ ሰው መትቶ አቈሰለው።

38 ከዚያም ነቢዩ ሄዶ ከመንገድ ዳር በመቆም፣ ንጉሡን ይጠባበቅ ጀመር። የራሱን መጠምጠሚያ ወደ ታች አውርዶ ዐይኖቹን በመሸፈንም፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ አደረገ።