1 ነገሥት 20:34-40 NASV

34 ቤንሀዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው።አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው።

35 ከነቢያት ልጆች አንዱ ጓደኛውን በእግዚአብሔር ቃል ታዞ፣ “ምታኝ” አለው፤ ሰውየው ግን ፈቃደኛ አልሆነም።

36 ስለዚህም ነቢዩ፣ “ለእግዚአብሔር ባለ መታዘዝህ፣ ከእኔ ተለይተህ እንደሄድህ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ሰውየው ከሄደ በኋላ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።

37 ነቢዩም ሌላ ሰው አግኝቶ፣ “እባክህ ምታኝ” አለው። ስለዚህ ያ ሰው መትቶ አቈሰለው።

38 ከዚያም ነቢዩ ሄዶ ከመንገድ ዳር በመቆም፣ ንጉሡን ይጠባበቅ ጀመር። የራሱን መጠምጠሚያ ወደ ታች አውርዶ ዐይኖቹን በመሸፈንም፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ አደረገ።

39 ንጉሡ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ፣ ነቢዩ ጠርቶት እንዲህ አለው፤ “እኔ አገልጋይህ በተፋፋመው ጦርነት መካከል ገብቼ ሳለሁ፣ አንድ ሰው ምርኮኛ ይዞ መጥቶ ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ በገመዱ ትገባለህ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ’ አለኝ።

40 ‘ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።’ ”የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ራስህ ፈርደሃል፤ ይኸው ይፈጸምብሃል” አለው።