40 እንዲሁም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችንና ድስቶችን ሠራ፤ኪራምም በዚህ ሁኔታ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንደሚከተለው ፈጸመ፤
41 ሁለቱን ምሰሶዎች፣በምሰሶዎቹ አናት ላይ በክብ ቅርጽ የተሠሩ ሁለት ጒልላቶችን፤በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን በክብ ቅርጽ የተሠሩትን ሁለት ጒልላት ያስጌጡትን ሁለት መረቦች፤
42 በምሰሶዎቹ አናት ላይ ያሉትንና ክብ ቅርጽ የያዙትን፣ በሁለት ረድፍ የተቀረጹትን መረቦች፣ የሚያስጌጡትን አራት መቶ ሮማኖች፤
43 ዐሥሩን የዕቃ ማስቀመጫዎች፣ ከዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎቻቸው ጋር፤
44 ገንዳውንና በሥሩ ያሉትን ዐሥራ ሁለት በሬዎች፤
45 ድስቶችን፣ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን።ኪራም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት እንዲውሉ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለና ከሚብረቀረቅ ናስ ነበር።
46 ንጉሡም እነዚህን በማቅለጥ በሸክላ ቅርጽ ውስጥ ፈሰው እንዲወጡ ያደረገው በሱኮትና በጻርታን መካከል ባለው በዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር።