1 ነገሥት 8:13-19 NASV

13 እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።”

14 መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ።

15 ከዚያም እንዲህ አለ፤“ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤

16 ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠ ራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’

17 “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤

18 እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስበሃልና፣ ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፤

19 ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ ሳትሆን፣ ከአንተ የሚወለደው ልጅህ ነው፤ አዎን ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው።’