1 ነገሥት 8:18-24 NASV

18 እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስበሃልና፣ ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፤

19 ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ ሳትሆን፣ ከአንተ የሚወለደው ልጅህ ነው፤ አዎን ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው።’

20 “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ፈጽሞአል፤ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቻለሁ፤ በእስራኤል ዙፋን ተቀምጫለሁ፤ እንዲሁም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ።

21 ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”

22 ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣

23 እንዲህ አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በፍጹም ልባቸው ጸንተው ለሚኖሩ አገልጋዮችህ ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ጽኑ ፍቅርህን የምትገልጥ አንተ ነህ፤ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እንዳንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤

24 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቀሃል፤ በአፍህ ተናገርህ፤ ይህንኑም በዛሬው ዕለት በእጅህ ፈጸምኸው።