1 ነገሥት 8:37-43 NASV

37 “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት፣ ዋግ ወይም አረማሞ በሚከሠትበት፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚወርድበት ወይም በምድራቸው ውስጥ ባሉት ከተሞቻቸው ጠላት ቢከባቸው እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚመጣባቸው ጊዜ፣

38 ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንኛውም ሰው የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣

39 በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። አንተ ብቻ የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ሁሉ ክፈለው፤

40 ይህም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩ ነው።

41 “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፣

42 ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣

43 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የጠየቀህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ ስምህን ዐውቀው፣ ሕዝብህ እስራኤል አንተን እንደሚፈሩት ሁሉ እንዲፈሩህ፣ እኔ የሠራሁትም ይህ ቤት በስምህ መጠራቱን እንዲያውቁ ነው።