1 ነገሥት 8:42-48 NASV

42 ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣

43 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የጠየቀህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ ስምህን ዐውቀው፣ ሕዝብህ እስራኤል አንተን እንደሚፈሩት ሁሉ እንዲፈሩህ፣ እኔ የሠራሁትም ይህ ቤት በስምህ መጠራቱን እንዲያውቁ ነው።

44 “ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፣

45 ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ርዳቸውም።

46 “መቼም ኀጢአት የማይሠራ የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ አንተም ተቈጥተህ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነው ምድሩ ማርኮ ለሚወስደው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣

47 ተማርከው በሚኖሩበት አገር ሳሉ ልባቸው ቢመለስ፣ በተማረኩበትም ምድር ሆነው ንስሓ ቢገቡና ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣

48 እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቹ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደዚህች ምድር ወደ መረጥሃትም ወደዚህች ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣