1 ነገሥት 8:50-56 NASV

50 በአንተ ላይ ስለሠሩት ኀጢአት፣ አንተንም ስለ በደሉህ በደል ሁሉ ሕዝብህን ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ።

51 ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና።

52 “አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤

53 አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካኝነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”

54 ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጒልበቱ ተንበርክኮ ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ።

55 ከዚያም ቆሞ መላውን የእስራኤልን ጉባኤ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ ሲል መረቀ፤

56 “በሰጠው ተስፋ መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን ለሰጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ በባሪያው በሙሴ አማካይነት ከተሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ አንድም ቃል አልቀረምና።