2 ነገሥት 11:10-16 NASV

10 ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሥ ዳዊትን ጦርና ጋሻ ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።

11 ወታደሮቹም እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን ይዘው፣ ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።

12 ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጠው፣ መንገሡን ዐወጀ፤ ኢዮአስም ተቀብቶ ነገሠ። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።

13 ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደች።

14 እነሆ፤ በወጒ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀዳ፣ “ይህ ክዳት ነው! ክዳት ነው!” በማለት ጮኸች።

15 ካህኑ ዮዳሄም ጭፍሮቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤ የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ በሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤት መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር።

16 ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት ስፍራ ስትደርስ፣ ይዘው እዚያው ገደሏት።