2 ነገሥት 12:16-21 NASV

16 ስለ በደል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ገንዘብ ግን የካህናቱ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይገባም ነበር።

17 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጣ፤ ጌትንም አደጋ ጥሎ ያዛት። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ፊቱን አዞረ።

18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ግን አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮሆራም፣ አካዝያስ ለእግዚአብሔር ቀድሰው የለዩአቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ፣ እርሱ ራሱ የቀደሳቸው ስጦታዎች እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ሰብስቦ ለሶርያ ንጉሥ ለአዛሄል ላከለት፤ አዛሄልም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።

19 ኢዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመው ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

20 ሹማምቱም በእርሱ ላይ ዐመፁበት፤ ቊልቊል ወደ ሲላ በሚወስደው መንገድ ላይ በቤት ሚሎ ገደሉት።

21 ገዳዮቹ ሹማምትም የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ነበሩ። እርሱም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አሜስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።