2 ነገሥት 12:2-8 NASV

2 ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

3 ይሁን እንጂ የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በእነዚህ ቦታዎች መሠዋቱንና ማጠኑን እንደ ቀጠለ ነበር።

4 ኢዮአስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለቤተ መቅደሱ የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ።

5 እያንዳንዱም ካህን ገንዘቡን ከገንዘብ ያዡ እጅ ይቀበል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል።”

6 ይሁን እንጂ እስከ ሃያ ሦስተኛው የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን አላደሱም ነበር።

7 ስለዚህ ኢዮአስ ካህኑን ዮዳሄንና ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ፣ “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ያላደሳችሁት ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ ቀጥሎም፣ “ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል እንጂ ከገንዘብ ያዦች አትቀበሉ” አላቸው።

8 ካህናቱም ከእንግዲህ ከሕዝቡ ገንዘብ ላለመሰብሰብና ቤተ መቅደሱንም ራሳቸው ላለማደስ ተስማሙ።